ውልደትና ዕድገት
የወላጆቹ የበኩር ልጅ የሆነው ጋዜጠኛ ኤልያስ ጉዲሳ ውልደትና ዕድገት ሳሪስ - አዲስ አበባ ነው።
የአንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ቀለም የቀሰመው ሰኔ ዘጠኝ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው ነፋስ ስልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በዚያም አላበቃም። የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ውጤቱ መልካም በመሆኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ዘልቋል።
የሥራ ዓለም - የጋዜጠኝነት ሕይወት ጅማሮ
ኤልያስ - የጋዜጠኝነት ሕይወት ፈልግን መከተል የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለ ነበር። ትምህርት ቤቱን በመወከል ከአቻ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ጋር ተወዳዳሪ ሆኖ የጥረቱን ፍሬዎች አይቶበታል። ተሸላሚ ለመሆን በቅቶበታል።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳለም የሬዲዮ ድራማዎችን በመፃፍ የሥነ ጽሑፍ በረከቶቹን እነሆኝ ማለት ጀመረ። የቀለም ትሩፋቶቹ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ተወስነውም አልቀሩም። እ.ኢ.አ. በ1989 ዓ.ም በወቅቱ ተወዳጅ የነበረው “የቅዳሜ መዝናኛ ዝግጅት” ስቱዲዮ ደረሰ።
በማኅበራዊና የፍቅር ሕይወቶች ዙሪያ የሚያጠነጥነው የራዲዮ ድራማው የአየር ሞገድ አሳብረው አደባባይ ዋሉ። ከአድማጮች ጆሮ ዘለቁ። ለሶስት ሳምንታት በተከታታይ በኢትዮጵያ ራዲዮ ሞገድ ላይ ናኙ።
የቀለም ጠብታው ጭማቂዎቹ ከራዲዮ ጣቢያው የመጀመሪያውን የሥራ ዋጋ ክፍያ፤ ከአድማጮች አበረታች ግብረ ምላሾችን አስገኘለት። ከወቅቱ የመጽሔት አሳታሚዎች ጋርም ለትውውቅ አበቁት።
የሕይወት ጥሪውን ተከትሎ ለሶስት ወራት በተከታታይ ለጋዜጦችና መጽሔቶች ጽሑፎችን ማቅረብ ጀመረ። ከሩብ ዓመት በኋላ ራሱን ችሎ የሕትመት ውጤቶችን ለአንባቢያን ለማድረስ ተነሳሳ።
የመጀመሪያ የሕትመት ውጤቱ የሆነችው “ቃል ኪዳን” ጋዜጣ አሳታሚ ሆነ። የጋዜጣይቱ ተነባቢነት እየጨመረ መጣ። ቃል ኪዳን - በሳምንት አንዴ ከመውጣት በሳምንት ሁለቴ አንባቢያን እጅ መግባት ጀመረች።
ሲልም፤ እ.ኢ.አ. በ1990 የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ሲከፈት ፓለቲካ ተኮር የሆነችውን “ትኩሳት” ጋዜጣ አከለ። ትኩሳት - በገቢም በተደራሽነትም ስኬታማ ለመሆን በቃች። ከሁለት ዓመታት በኋላ “ረመጥ” ጋዜጣን ሶስተኛ የሕትመት ውጤቱ አድርጎ ማሳተም ያዘ።
ኤልያስ - በዚህም አላበቃም። እ.ኢ.አ. በ1994 “ቃል ኪዳን” ጋዜጣ ላይ “ቃል ኪዳን” መጽሔትን ጨመረ። የጋዜጦቹና መጽሔቱ ሕትመት ውጤቶችም ለበርካታ ጋዜጠኞች የሥራ ዕድሎችንም ከፍቷል።

Source: Elias Gudisa
ሆኖም ጥቂት ቆይቶ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አሳታሚዎች በአንድ የሕትመት ዘርፍ ብቻ መርጠው እንዲሠሩ የሚል አስገዳጅ ድንጋጌ በማውጣቱ ጋዜጦቹን ዘግቶ በ”ቃል ኪዳን” መጽሔት ሕትመት ብቻ ተወሰነ።
ቀደም ሲል በማኅበራዊ ሕይወት ላይ ብቻ ታተኩር የነበረችው ቃልኪዳን በጥምረት ፖለቲካዊ ጉዳዮችንም አካትታ ይዛ መውጣት ጀመረች። ፖለቲካዊ ትኩረቷ ግና መዘዞችን አስከተሉ።
ኤልያስን ወደ አገረ ኬንያ ለስደት ዳረጉ።
ከ2 ዓመታት ከ11 ወራት በኋላም ለአገረ አውስትራሊያ አበቁ።
ኑሮ በአውስትራሊያ
ኤልያስ - የአውስትራሊያን ቀይ አፈር ለመጀመሪያ ጊዜ የረገጠው የምዕራብ አውስትራሊያ ክፍለ አገር ዋና ከተማ ፐርዝ ሲሰፍር ነው። እምብዛም ሳይቆይ ግና በአራተኛ ወሩ የቪክቶሪያ ክፍለ አገር ዋና ከተማ ወደ ሆነችው ሜልበርን አቀና።
ሜልበር ከአውስትራሊያ ክፍለ አገራት ሁሉ የበርካታ ኢትዮጵያውያን መኖሪያ በመሆኗ የጋዜጠኝነት ሕልሙን ዕውን ለማድረግ አለመ።

Elias Gudisa Source: Elias
የ “ቃል ኪዳን” መጽሔትን በአገረ አውስትራሊያ “ሀ” ብሎ ጀመረ። ይዞ የተነሳው ዓላማ ለገቢ ማስገኛነት ሳይሆን የሙያ ፍቅርን በመወጣት ለራስ ማኅበረሰብ ግልጋሎትን ለማበርከት ነው።
እስካሁን አራት የቃል ኪዳንን ዕትሞችን ለአንባቢያን አቅርቧል።

Source: Elias Gudisa
ኑሮን ለማሸነፍ ለአንድ የምግብ ምርት ኢንዱስትሪ ግልጋሎት ሰጪ ኩባንያ Site Manager ሆኖ እየሠራ ይገኛል።
ለSBS አማርኛ ክፍል በሪፖርተርነት ሙያዊ አስተዋጽኦ እያበረከተ አለ።