ገብረመድኅን አርአያ የተወለዱት አድዋ ከተማ ነው። አባታቸው ብላታ አብርሃ መርዕድ ገበሬና አንጥረኛ ነበሩ። የአባታቸው - አባት - አያታቸው የአፄ ዮሐንስ አራተኛ ጓደኛ የነበሩ ናቸው። እናታቸው ታዋቂና በእርሻ ተዳዳሪ የነበሩት ብላታ ገብሩ ልጅ ናቸው።
ወላጆቻቸው አራት ልጆችን ከአብራካቸው ከፍለው ያፈሩ ሲሆን፤ ገብረመድኅን የመጨረሻው አራተኛ ልጅ ናቸው።
የልጅነት ሕይወት
ገብረመድኅን ሰብዕናቸውን ለመቅረፅ አባታቸውን በአርአያነት እየተመለከቱ አላደጉም። አባታቸው በሞት የተለዩዋቸው ገና ሕጻን ሳሉ ነበር።
ይሁንና የእናታቸው ወንድም የነበሩት ቀኝ አዝማች አራአያ ገብሩ እንደ ልጃቸው አድርገው ሊያሳድጉ ወሰዷቸው። አራተኛ ክፍል እንደደረሱ አጎታቸው የመንግሥት ሠራተኛ ነበሩና ወደ አክሱም ተዛወሩ። ገብረመድኅን አጎታቸውን ተከትለው አራተኛና አምስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን አክሱም ከተከታተሉ በኋላ ወደ አድዋ ተመለሱ። የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አድዋ ንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት አጠናቀቁ።
ከአድዋ ወደ አዲስ አበባ
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ከአድዋ ንግሥተ ሳባ ትምህርት ቤት እንደጨረሱ ያቀኑት ወደ አዲስ አበባ ነው። ከዚያም ከንግድ ሥራ ትምህርት ቤት አጠናቅቀው ተመረቁ የገንዘብ ሚኒስቴር ተቀጣሪ በመሆንም ለመንግሥት ሠራተኛነት በቁ።
አዲስ አበባ በመንግሥት ሠራተኛነታቸው ብቻ ረግተው አልቆዩም። ወቅቱ የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት ሊፈነዳ ዋዜማ ላይ የነበረበትና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ንቅናቄ የተቀጣጣለበት ነበር።
የማንነት ፖለቲካ የአፍላ ግራ ከረሮች አጀንዳ ነበርና ገብረመድኅን አርአያ የትግራይ ተወላጅነታቸው ዘር ተመዝዞ በቀድሞው የሕወሓት ሊቀመንበር በአሁኑ ወቅት የትግራይ ዲሞክራሲያዊ ትብብር ሊቀመንበር የሆኑት አረጋዊ በርሄ በድርጅት አባልነት ተመለመሉ።
የየካቲት ‘66ቱ አብዮት ፈነዳ። በ1967 ማኅበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ (ማገብት) ሲመሰረት ገብረመድኅን አርአያ የማገብት አባል ሆኑ።
ከአዲስ አበባ ወደ በረሃ
ወደ በረሃ ገብተው በወቅቱ በሥልጣን ላይ የነበረውን የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግን ለመታገል በመዘየድ ወደ ትግራይ የሥራ ዝውውር ጠየቁ። ተፈቀደላቸው።
ትግራይ ገብተው ግና ከመንግሥት ሥራቸው ይልቅ የድርጅታቸው ሥራ ላይ አተኮሩ። አባላት ምልመላው ላይ አብዝተው ሠሩ።እንቅስቃሴያቸው በመንግሥት ዓይን ውስጥ መግባቱን በድርጅታቸው በኩል ተጠቆሙ። ሳይቀደሙ ለመቅደም ኮብልለው ወደ በረሃ ወረዱ።
በረሃ እንደደረሱ በሕክምና ዘርፍ ሥልጠና ተሰጣቸው። ብዙም ሳይቆዩ የንግድ ሥራ ትምህርት ቤት ምሩቅነታቸው ፍሬ ተመዝኖ የማኅበራዊና ምጣኔ ሃብት ዘርፍ ተመደቡ።
ከሕወሓት ወደ አገር ቤት
አቶ ገብረመድኅን በሕወሓት ታጋይነት 15 ዓመታትን ካስቆጠሩ በኋላ ተነጥለው ወጡ። ሰነባብተው እጃቸውን ለኢሕዲሪ መንግሥት ሰጡ። አገር ቤት ገብተውም በብዙኅን መገናኛ ከቀድሞ የትግል ጓዳቸው አቶ አብርሃም ያየህ ጋር ሆነው የሕወሓትን አሉታዊ ገፅታዎችን ገለጡ።
ብዙም ሳይቆዩ ግና በሕወሓት የሚመራው ኢሕአዴግ የኢሕዲሪን መንግሥት ገርስሶ በእግሩ ተተካ። የአቶ ገብረመድኅን ዕጣ ፈንታም ስደት ሆነ። በኬንያ አቋርጠው ኡጋንዳ ገቡ።
ከኡጋንዳ - አውስትራሊያ

Gebremedhin Araya Source: Courtesy of PD