ፊደል ቆጠራ
የአቶ ንብረት አባት የሴት አያት የቤተክርስቲያን የአቋቋም መምህርት ነበሩ። ከዚያም ጋር ተያይዞ በተወሰኑ የቤተሰብ አባላት ዘንድ ዳዊት ደገማ ላይ ያሉት ንብረት፤ ለቅስና ይበቁ ይሆናል የሚል ተስፋ ጭሮ፤ እምነትም አሳድሮ ነበር።
ሆኖም፤ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የወቅቱ ዘመናዊ ትምህርት ፖሊሲ ሳቢያ ከቄስ ትምህርት ቤት ወደ አስኳላ ዘለቁ።
በሞጣ እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማሩ።
ዕጩ መኮንንነት
በደብረ ማርቆስ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ 11ኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ ለሐረር ጦር አካዳሚ ዕጩ መኮንን መልማዮች ትምህርት ቤታቸው ተገኙ። ስለ ወታደራዊ ሕይወትና ዘላቂ የቀለም ትምህርት ዕድሎች ገለጣ አደረጉ።
አቶ ንብረት በገለጣው ልባቸው ተማረከ። ለዕጩ መኮንንነት የሚያበቃ ፈተና ወሰዱ። ፈተናውን ካለፉት ስድስት ተማሪዎች መካከልም አንዱ ሆኑ።
ይሁንና ውጤቱን የሰሙትና ልጃቸው ሐኪም እንጂ የጦር መኮንን እንዲሆን ያልወደዱት አባታቸው ቅሬታቸውን በቁጣ አዘል ቃል ገለጡ።
አቶ ንብረት ወደ ሐረር ጦር አካዳሚ ሳይሔዱ ቀሩ።
ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና እየተዘጋጁ ሳለ ሌላ አማራጭ ዕድል መጣ።
ወባ መከላከያ
የወባ መከላከያ ድርጅት ተወካዮች ድርጅቱ ለማቋቋም ስላሰበው የስልጠና ተቋምና የውጭ አገር ትምህርት ዕድሎችን አንሰተው አብራሩ።
አቶ ንብረት ቀልባቸው ተሳበ። ለፈተና ተቀመጡ። ከ33 ዕጩ ተወዳዳሪዎች የሚፈለገው አንድ ዕጩ ነበር። በፈተናው ውጤት ቀዳሚውን ሥፍራ ይዘው ተገኙ።
እምብዛም ሳይቆዩ ወደ ናዝሬት የወባ መከላከያ ድርጅት ማሰልጠኛ ማዕከል ገብተው ስልጠና ጀመሩ።
አብዮት
በወቅቱም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን ማለፋቸውን አወቁ። በውጤታቸው መሠረት ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት እየተሳናዱ ሳለ የ1966ቱ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮት ተከሰተ።
የኢትዮጵያ የመጨረሻው የዘውድ ሥርዓት ተገርስሶ ወደቀ። ወታደራዊ መንግሥት ተተካ።
የጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ከመላ አገሪቱ ማይምነትን ለማጥፋት የዕድገት በሕብረት የዕውቀትና ሥራ ዘመቻ አዋጅን አወጀ።
ብሔራዊ የዘመቻ ጥሪ ቀረበ።
አቶ ንብረት ግና ዘመቻውን እምቢኝ አሉ።