የስደት ሕይወት ፈታኝነት የአደባባይ ምስጢር ነው። ለስኬት ለበቁት እንኳ እሾሃህን የተላበሰ ጽጌረዳ ነው። ደራሲ ታክሎ ተሾመ፤ በአገረ ሱዳን የስደት ሕይወታቸው አገር ቤት ትተውት የወጡት ልጃቸው ናፍቆት ተጨምሮ፤ ሌሎች በርካታ ፈተናዎች ተቀንሰው፤ በማሽላ ቆረጣና ውኃ ሽያጭ ለመተዳደር ግድ ተሰኝተዋል። ዘግየት ብለው የአንድ መኪና መለዋወጫ ሱቅ ሥራ አስኪያጅ ለመሆን እስከበቁ ድረስ።
ቤተሰብ ምስረታ
አቶ ታክሎ የሱዳንን ድንበር ተሻግረው ለስደተኝነት የተዳረጉት ድርጅታቸው ኢሕአፓ የደርግ አገዛዝ ዒላማ በመሆኑ ልባቸው ተገዢ የነበረው ለኢሕአፓ ፍቅር እንጂ ለተቃራኒ ፆታ አልነበረም።
ታላቁ መፅሐፍ "ለሁሉም ጊዜ አለው" እንዲል፤ፍቅራቸውን ለዛሬዋ ባለቤታቸው ወ/ሮ ገበያነሽ አጋሩ።
ቀለበት ተሳሰሩ።

አዲሶቹ ባለ ቀለበቶች ወራት አስቆጥረው የመጀመሪያ ልጃቸውን አፈሩ።
ስሟን "አበባ" ሲሉ ሰየሙ።
ጉዞ ወደ አውስትራሊያ
አውስትራሊያ አቶ ታክሎን፣ ባለቤታቸውን ወ/ሮ ገበያነሽንና ልጃቸውን አበባን ተቀበለች።
አዲሱ መኖሪያቸውም በጣት የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ይኖሩባት የነበረችው ሆባርት - ታዝማኒያ ሆነ።

እምብዛም ሳይቆዩ ግና እስካሁንም ወደ አሉባትና በርካታ ኢዮጵያውያን ወደ ሚኖሩባት ሜልበርን ከተማ ጓዛቸውን ሸክፈው ከቤተሰባቸው ጋር ከተሙ።
በዓመታት ቆይታቸው ቤተሰባቸው በልጆች በረከት ተመላ። ቁጥሩም በረከተ።

ደራሲ ታክሎ ተሾመ፤ በግል ኑሯቸው ደስተኛ እንደሆኑ ይገልጣሉ።
'የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አባላት ማኅበራዊ አኗኗርና አገራዊ ተሳትፎ ጥንካሬው የላላ ነው' የሚል አተያይም አላቸው።






