የዘንድሮ ዘመን መለወጫን በምናከብርበት ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ እና ወገኖቻችን ኢትዮጵያውያን የምናስባቸው እና የምንመኛቸው ብዙ ነገሮች አሉ።
የዕንቁጣጣሽ በዓል መሠረቱ ታላቋ ማክዳ ንግሥተ ሳባ ከእየሩሳሌም በተመለሰችበት ግዜ መሳፍንቶቿ “እንኳን በደህና ተመለሽ” ለማለት የዕንቁ እና የከበሩ ጌጣጌጥ በስጦታ ስለ ሰጥዋት ነው።
ይህ የዘመን መለወጫ በዓል እና የዓመታት፥ የወራት፥ የቀናት፥ የሰዓት፥ አቆጣጠራችን ከጥንት አባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የሚያኮራ ልዩ ባሕላችን ነው።
የኢትዮጵያዊነት ልዩ ኩራታችን ነው።
ዘመን ሲለወጥ ያለፈውን በማጤን እና አምላክን በማመስገን፥ የሚመጣውንም በተስፋ እና በጸሎት መቀበል የቆየ ልማዳችን ነው።
በሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ።
ሕዝባችን ሰላሙን እንዲያገኝ፥ ከችግር፥ ከመከፋፈል፥ ከስደት እንዲ ወጣ የሁላችንም ጸሎት ሊሆን ይገባል።
ፈጣሪ ላደረገልንም ምስጋና ማቅረብ ተገቢ ነው።
በሚቀጥሉት ቀናት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተፈጽሞ ይመረቃል። የኢትዮጵያ ነገሥታት ከጥንት ጀምሮ ዓባይን ለመገደብ ምኞት ነበራቸው።
በአያቴ በግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት የዓባይ ተፋሰስ ግድቦች ጥናት ተደርጎ በዘመኑ የነበረን የአቅም ማነስና የዓለም ፖለቲካዊ አሰላለፍ ስላልፈቀደ “ልጆቻችን ወደፊት ይሰሩታል” ብለው ምኞቱን እና ጥናቱን ለመጪው ትውልድ አስተላልፈዋል።
ከዘመናት በኋላ በቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትሮች በአቶ መለስ ዜናዊ አነሳሽነት እና በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቀጣይነት፥ ከዛም በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ፈፃሚነት ይህ የአባቶቻችን ሕልም እውን ሆኗል።
የአገር ጥቅም ከⶒለቲካ ጥቅም እና ስሜት በላይ በመሆኑ ለነዚህ መሪዎችና ከሁሉም በላይ ከሚበላው ቀንሶ ለዚህ ታላቅ የአገር ኩራት ለሆነ ግድብ ያዋጣው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ምስጋና ይገባል።
አንድ ስንሆን ሳንለያይ ብዙ መሥራት እንደምንችል ይህ ትልቅ ምሳሌ ነው። እግዚአብሔርም የግርማዊ ጃንሆይን ሕልም ተሠርቶ ስላሳየን ስሙ ምስጉን ይሁን።
ይህ አዲስ ዓመት ለአገራችን ለኢትዮጵያ እና ለልጆቿ የሰላም የጤንነት የሕዳሴ ያድርግልን።
ዘመነ ማርቆስ 2018 ዓመተ ምሕረትን ልዑል እግዚአብሔር ይባርክልን።
ለዓመት ዓመት ያድርሰን።