Watch FIFA World Cup 2026™

LIVE, FREE and EXCLUSIVE

ምልሰታዊ ምልከታ 2022፤ሔርሞንና ኤደን፤ የአልኮል ሱስና የፍቅር ፈተና

Hermon Eden 4.jpg
Hermon Gashaw (L), and Eden Roma (L). Credit: H.Gashaw and E.Roma

ሔርሞን ጋሻውና ኤደን ሮማ ከሱስ በመላቀቅና በፍቅር ፀንቶ በመቆየት ተፈትነዋል። ሔርሞን ከአልኮል ሱስ ለመላቀቅ፤ ኤደን በገደብ የለሽ ፍቅር የሕይወቷ ማዕከል ለመሆን የበቃውን ሔርሞንን ለመታደግ።


Published

By Kassahun Seboqa Negewo

Source: SBS



Share this with family and friends


ሔርሞን ጋሻውና ኤደን ሮማ ከሱስ በመላቀቅና በፍቅር ፀንቶ በመቆየት ተፈትነዋል። ሔርሞን ከአልኮል ሱስ ለመላቀቅ፤ ኤደን በገደብ የለሽ ፍቅር የሕይወቷ ማዕከል ለመሆን የበቃውን ሔርሞንን ለመታደግ።


ፍቅር ለስኬት ሲበቃ በጣፋጭ ሕይወት ውስጥ ያኖራል። ክሽፈት ሲገጥመው ለልብ ስብራት ይዳርጋል።

በሁለቱም መንገዶች የሕይወት ስንክሳሮች ብዙ ናቸው።

ፍቅር ስሜትን ያውካል፣ የማንነት ዕሴቶችን ይፈትናል፣ ኅሊናን ይሞግታል፣ ለተስፋ መቁረጥ ይዳርጋል፤ ሲልም የሰላምና የጠብም ምንጭ እስከ መሆን ያደርሳል።

የእውነተኛ ፍቅርን ጣዕም ለማጣጣምና ለመኖር ሕይወቱንም ለመኖር የሚበቁት ጥቂቶች የሚሆኑትም ለዚህ ነው።

ሔርሞንና ኤደን ከጥቂቶቹ የሚደመሩ ናቸው።

"ጠጪ ከሚባሉት በላይ የምጠጣ ነበርኩ"

ሔርሞን መጠጥ የለመደውና ለሱሰኝነትም የበቃው ኢትዮጵያ ሳለ ነው። መነሻውም የቤት አረቄ ነው።

እ.አ.አ በ2015 ወደ አውስትራሊያ ከመጣ በኋላ ግና "ሰው ኑሮውን ይመስላል" እንዲሉ ወደ ቢራና ውስኪ ተሸጋገረ።

ጠጥቶ ማሽከርከር በብርቱ ጥብቅ የሆነባት አገረ አውስትራሊያ ሕግ ግና አላገደው።

እንደ አያሌ ዕለተ ሕይወቱ ሁሉ በአንዲቷ ቀን ከማለዳው መጠጣት ጀመረ። ከቀትር በኋላ ሠርግ ቤት አከለበት።

ምሽት ላይ ከአንድ የመዝናኛ ቤት የማሳረጊያ አልኮል ተጎንጭቶ እንደወጣ መኪናውን አጋጭቶ ለሆስፒታል በቃ።

እግሮቹ በጣም ተጎድተው ስለነበርም በምርኩዝ ለመሔድ ግድ ተሰኘ።

Hermon .jpg
Hermon Gashaw. Credit: H.Gashaw.

"እሹ ታገኛላችሁ፤ አንኳኩ ይከፈትላችኋል"

ኤደን ሮማ የሔርሞን እህት ጓደኛና የቤተክርስቲያን ዘማሪ ናት።

የመኪና አደጋውን አስደንጋጭ ዜና ሰምታ ከእህቱ ጋር ሔርሞንን ጥየቃ ወደ ሆስፒታል ሔደች።

የደረሰበትን ጉዳት ስታይ ልቧ አዘነ። ከዚያ በፊት ተሰምቷት የማታውቀው ዓይነት ስሜትም ውስጧን አወከው።

ከሆስፒታል ተሰናብታ ቤቷ ከተመለሰች በኋላም ስለ ሔርሞን ማሰቧን ቀጠለች።

ዕሳቤዋ ውስጥ ገዝፎ ይታያት የነበረው የሕመምተኛ ፊቱ፣ በጄሶ ተጠቅልሎ የተሰቀለ ጉዳተኛ እግር፣ በሕመምና በድካም የዛለ አካል ሳይሆን፤ ከቶውንም ማግኔታዊ ስህበት ያለው ወጣት ገፅታ ነበር።

ወደ ውስጧ ተመለከተች። ስሜቷን ጠየቀች።

አዕምሮዋ ስሜቷ በርህራሄ መመላቱን አመላከታት።

ልቧ ፍቅር ላይ መውደቋን ትንፋሽን ቁርጥ - ቁርጥ በሚያደርግ ትርታው ነገራት።

ልቧን አመነች።

"ፍቅር ይዞኛል" ብላ ለራሷ አረጋገጠች።

እውነት ነበር።

***

ሔርሞንም በበኩሉ በኤደን ውብ ገፅታ ልቡ መማለሉ ገባው።

ከአንደበቷ ይፈልቁ የነበሩ 'አይዞህ ባይ' ቃላት ለጆሮ የሚጥም ጥዑም የሙዚቃ ቃና ሆነው ተሰሙት።

"በሕይወቴ እንዲህ ያለ ሁኔታ ገጥሞኝ አያውቅም። ይህች ልጅ ልታመልጠኝ አይገባም" ሲል ለራሱ ነገረ።

እንዳታመልጠውም ብዙ ርቀት ተጓዘ...


Latest podcast episodes

Follow SBS Amharic

Download our apps

Watch on SBS

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service

Stream now