30 የሽልማት ዘርፎችን ያቀፈው ሥነ ሥርዓት የተካሔድው ዓርብ መጋቢት 6 / 2016 / ማርች 15, 2024 በክራውን ፖላዲየም ነው።
የSBS አማርኛ ፕሮግራም ጋዜጠኛ ካሣሁን ሰቦቃ ነገዎና ጋዜጠኛ ሩቺካ ታልዋር ለሜልበርን ፕሬስ ክለብ በመድብለባሕል ጉዳዮችና ሚዲያ ዘርፍ በአውስትራሊያ ፕሮፌሽናል ጋዜጠኝነት ሙያ የላቀ ደረጃ ያለውን 29ኛውን የኩዊል የጋዜጠኛንት ልህቀት ሽልማት አሸናፊ ለመሆን የበቁት Detention to determination: Former Nauru detainee is now a ticket inspector on Melbourne Metro በሚል ርዕስ የኢትዮጵያዊቷን ቤተልሔም ጥበቡ የናሩ ዕገታ ማዕከል ስቃይና የመንፈስ ፅናት አስመልክተው ባቀረቡት መጣጥፍ ነው።
የSBS አማርኛ ፕሮግራም መጣጥፍ ከABC News፣ Herald Sun እና Guardian Australia ጋር ተወዳድሮ ለአሸናፊነት ብቁ የሆነበት ምክንያት "አስደናቂው መጣጥፍ የአውስትራሊያን ቀጪ የኢሚግሬሽን ማዕከል ፖሊሲዎች መርምሯል። ርዕሰ ጉዳዮ ብርቱ ነው፤ እንዲያም ሆኖ ግና ጋዜጠኞች ካሣሁን ነገዎ እና ሩቺካ ታዋር ጥርት ባለ ትረካቸው በጣሙን ሰብዓዊ የሆነ ታሪክ አቅርበዋል።

"በተለይም፤ በጀልባ የመጣችው የታሪኩ ማዕከል ጥገኝነት ጠያቂ ከቶውንም በጣሙን ግላዊ በሆነው ትርክት ተስፋ ቢስ ተደርጋ አልቀረበችም። አንባቢ ከናሩ ዕገታ ማዕከል ተነስቶ በመሸጋገሪያ ቪዛ እስከ አዲስ የሜትሮ ባቡር ቲኬት ተቆጣጣሪነት ሕይወት አዋኪ በሆነው ዘርፈ ብዙ ታሪክ ተስቦ ይገባል" የሚል የዳኞች አስተያየትን በማግኘት ነው።
በዕለቱ በ30 የተለያዩ የጋዜጠኝነት ሙያ ዘርፍ አሸናፊ የሆኑ የአውስትራሊያ ዋነኛ ፕሮፌሽናል ሚዲያ ዝነኛ ጋዜጠኞች ከወርቅ ኩዊል እስከ የሕይወት ዘመን ሽልማቶችን ተቀብለዋል።


