ኤልቪስ ፕሪስሊ በትወናው ማለፊያ ተዋናይ፤ በዘፈኖቹ "King of Rock and Roll" ተብሎ ተሞካሽቷል። የጥበብ ሥራዎቹ ከሞት በኋላ ሕይወት ሆነውታል። ለሙዚቃ አፍቃሪዎቹም ዋጋ የማይተመንባቸው የውብ ጊዜያት ውድ ትዝታዎች ሆነው አሉ። የጥበብ ባልደረቦቹም "Elvis" በሚል መጠሪያ የሙዚቃ ሥራዎቹንንና ግለ ሕይወቱን ነቅሰው በፊልም ሞገስ አላብሰውታል። ተዋናይት ሰናይት መብራህቱም በትወናው ዓለም የኤልቪስን ዘመን ከኤልቪስ ጋር በአጃቢ ድምፃዊነት የታሪክ ታዳሚ አድርጋናለች።
ተዋናይት ሰናይት ለኤልቪስ ፊልም ትወና የበቃችው ከትወና ሙያ ተወካዩዋ በደረሳት ጥሪ ነው።
እውነተኛውን የሥራ ዓይነት አላወቀችም።
ይሁንና ድምፅና ውዝዋዜን ያቀፈ መሆኑን ግና ተረድታለች።
ተወካይዋም ለ 30 ሰከንዶች ስትዘፍን መቅረፅ እንደሚፈልግ ሰናይትን ጠየቀ።
ሆኖም ለዘፈን እንግዳ ያልሆነችው ሰናይት ግር ተሰኘች።
ጥቂት አስባ ሴት ልጇ ኤላና ለቤተክርስቲያን የምታዜመው መንፈሳዊ ዜማ አዕምሮዋ ውስጥ መጣ።
"I have decided to follow Jesus
No turning back, no turning back...
ስትል አዜመች።
ተወካይዋ የሚፈልገውን አገኘ።
በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዕጩዎች ውስጥ ከተመረጡት 14 አፍሪካውያን ሴቶች አንዷ ሆነች።
ከ14ቱ 10ሩ ተሰናበቱ።
ሰናይትን ጨምሮ 4 ተፈላጊ ተዋናይቶች የኤልቪስ "'The Sweet Inspirations' አጃቢ ድምፃውያን ተሰኝተው የታሪካዊው ኤልቪስ ሙዚቃዊ ድራማ ፊልም ቀረፃ አካል ሆኑ።
ሰናይት የኢስቴል ብራውንን ገፀ ባህሪይ ተላበሰች።

ኮሎኔል ቶም ፓርከርን ተመስሎ የሚተውነው የኤልቪስ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቶም ሃንክስ ብሪስበን ሳለ በኮቪድ 19 በመያዙ የፊልም ቀረፃው ለተወሰኑ ወራት ተቋረጠ።
ከወራት በኋላ ቀረፃው ዳግም ቀጠለ።
ሰናይትና መላው የኤልቪስ ፊልም ተዋናዮች ወደ ትወና ተግባራቸው ተመለሱ።
እ.አ.አ በ2014 ተወጥኖ፣ በ2019 ለፊልም ፕሮጄክት መብቃቱ የተነገረለት ፊልም ጁን 23 አውስትራሊያ ውስጥ በይፋ ለሕዝብ ቀረበ።







