“ሰው በመማር ብቻ ይለወጣል ብዬ አላስብም” - አዲስ ዓለም ፀጋዬ

Addis Alem Tsegaye

Addis Alem Tsegaye Source: Supplied

*** ከ22 ማዞሪያ እስከ አውስትራሊያ


ወ/ሮ አዲስ ዓለም ፀጋዬ ዕትብታቸው የተቀበረው በትውልድ ቀዬአቸው አዲስ አበባ 22 ማዞሪያ ነው። ለቤተሰባቸው አራተኛ ልጅ ሲሆኑ፤ ከሶስት እህቶችና ሶስት ወንድሞቻቸው ጋር አንድ ማኅፀን ተጋርተዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በቀድሞው ቢትወደድ በአሁኑ መጠሪያው የካ ምሥራቅ ጮራ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም በቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አከናውነዋል።
Addis Alem Tsegaye
Addis Alem Tsegaye - Addis Abeba Source: Supplied
ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው በኋላ ሶስት ዕንቁጣጣሾችን እንዳሳለፉ ከወላጆቻቸው ተሰናብተው፤ ውቅያኖስ አቋርጠው ወደ አገረ አውስትራሊያ አቀኑ።

የኑሮ ጅማሮ በአውስትራሊያ

የአውስትራሊያን አፈር የረገጡት እ.አ.አ. በ2000 ዓ.ም. ሲሆን፤ አመጣጣቸው በጋብቻ ነው። ከአዲስ አበባ ተነስተው የመጀመሪያ ጎጆአቸውን የቀየሱትም ሜልበር ከተማ ላይ ነው።

ሜልበርንን በረገጡ በዓመቱ አዲስ ትዳራቸው በአፍላነት ሳለ የመጀመሪያ ሴት ልጃቸውን በጋራ አፈሩ። ሕይወታቸው ከልጅነት ወደ እናትነት፤ ከጎጆ ወጪነት ወደ ቤተሰብ መሪነት ተሻገረ።

በአዲስ አገር ከአዲስ ባሕልና ሰው ጋር መላመድ የአዋኪነቱን ያህል ማለፊያ በረከቶችም አሉት። አዲስ አበባ ላይ ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በኋላ የተለዩትን ትምህርት ሜልበርንና ብሪስበን ላይ ቀጥለው የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪዎቻቸውን አግኝተዋል።
Addis Alem Tsegaye
Gradution 2005 and 2019 Source: Supplied
ቤተሰባዊ ዕሴቶች

ወ/ሮ አዲስ ዓለም ከወላጆቻቸው ከወረሷቸው ዕሴቶች ውስጥ ለትምህርት ትልቅ ሥፍራ መስጠትን፣ ለሰዎች መልካም መስተንግዶ ማድረግንና በትዳር ሕይወት ዘልቆ መኖር ተጠቃሾች ናቸው።

እናትና አባታቸው 50ኛ የወርቅ ኢዩቢልዩ የጋብቻ ሥነ ሥርዓታቸውን ሲያከብሩ በአካል መገኘት መቻላቸው ለትዳር ሕይወታቸው የሞራል ኮምፓስ ሆኗቸዋል።

መጽሐፍ የማንበብ ፍቅርንም ከታላቅ ወንድማቸው ቀስመዋል።

የሴቶች ጉዳይ

በሕብረተሰብ ሕይወት ውስጥ ከሚያሳስቧቸውና ለማቃናትም ከሚጥሩባቸው ዘርፎች አንዱ የሴቶች ጉዳይ ነው።

ሴቶች በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ በሕብረተሰብ ሕይወት ውስጥ በጎ ተፅዕኖዎችን አሳድረው፤ ማለፊያ አሽራዎችን ትተው እንዲያልፉ ይሻሉ። ያበረታታሉ።

“ሴቶች በራሳችን ሙሉ እንደሆንን ማመን አለብን” ሲሉም ይመክራሉ።

በቃለ ነቢብ ብቻ ተውጠው የቀሩም ሳይሆን ከአምስት ዓመታት የሜልበርን ኑሯቸው በኋላ መኖሪያቸው ባደረጓት ብሪስበን ከተማ በአነስተኛ የሴቶች ቡድን ውስጥ የሴቶችን ጉዳይ ማዕከል አድርገው ከ70 ያህል ሴቶች ጋር ስልጠናን መውሰድና ማስተባበር ችለዋል።

ንግድና የባሕል አምባሳደርነት

የብሪስበን ከተማ ለወ/ሮ አዲስ ዓለም ሁለተኛ ልጃቸውን ወደ ዓለም ያመጡበት፣ የመኖሪያ አድራሻቸው የሚገኝበት ብቻ ሳትሆን በካፌና የኢትዮጵያ ባሕላዊ ምግብ ቤት የንግድ ገቢ ማፍሪያም ናት።

ከመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶች ሠራተኝነት በኋላ በ2015 ፊታቸውን ወደ ንግዱ ዓለም ሲያዞሩ አንዱ ምክንያታቸው የቡና ምንጭ የሆነችውን ውድ አገራቸውን ኢትዮጵያ ማስተዋወቁንም በልባቸው ይዘው ነው።

ወደ ባሕላዊ ምግብ ቤት ሥራ ከማለፋቸው በፊትም የንግድ ሥራቸውን ያሟሹት አሁንም ድረስ ግልጋሎት በመስጠት ላይ ባለው addiscoffee.com.au የኦንላይን ቡና ሽያጭ ነው።
Addis Alem Tsegaye
Source: Addis Coffee
እርግጥ ነው፤ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እንደተቀረው ዓለም ሁሉ አውስትራሊያን ሲያጠቃ የእሳቸውንም ንግድ ጎሽሞ አልፏል።

ኢትዮጵያና አውስትራሊያ

በጋብቻ፣ በሥራ፣ በትምህርትም ሆነ በስደት ከትውልድ አገር ርቆ መውጣት በዘርፈ ብዙ መልኩ የአብራክ ክፋይ የሆኑ ልጆችን ጨምሮ ማንነትን ይፈትናል።

ወ/ሮ አዲስ ዓለምን እየሞገቱ ካሉ ፈተናዎች አንዱ ነው። ይትባሃሉ “ኢትዮጵያዊ ማንነቱን ነብር ዝንጉርጉርነቱን መለወጥ ያቻለዋልን?” እንዲል።

“ዞሮ ዞሮ ከቤት…” እንዲባልም ዕሳቤያቸው ከሰመረ ቀሪ ሕይወታቸውን ከባለቤታቸው ጋር ማጣጣም የሚሹት አገረ ኢትዮጵያ ላይ ነው።

አውስትራሊያ ከበረከቷ አብዝታ የቸረቻቸው አገር መሆኗንም በመጥቀስ “ኢትዮጵያም አውስትራሊያም ቤቶቻችን ናቸው” በማለት የግለ ታሪክ ወጋቸውን ይቋጫሉ።   


Share
Follow SBS Amharic

Download our apps
SBS Audio
SBS On Demand

Listen to our podcasts
Independent news and stories connecting you to life in Australia and Amharic-speaking Australians.
Ease into the English language and Australian culture. We make learning English convenient, fun and practical.
Get the latest with our exclusive in-language podcasts on your favourite podcast apps.

Watch on SBS
SBS World News

SBS World News

Take a global view with Australia's most comprehensive world news service