ውልደትና ዕድገት
የትውልድ ከተማቸው ደብረ ዘይት ብትሆንም፤ ገና የአራት ዓመት ሕጻን ሳሉ ነበር ለአዲስ አበባ ኑሮ ጉዟቸውን ከወላጆቻቸው ጋር ያቀኑት።
ወላጆቻቸው እሳቸውን ብቻ አላፈሩም። ከአምስት እህቶችና አንድ ወንድም ጋር በደም አቆራኝተዋቸዋል።
የአዲስ አበባ ኑሯቸውንም በቦሌ ክፍለ ከተማ ቆርቁረዋል።
ወጣቱ አዳሙ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው የአዲስ አበባን ውኃ ጠጥቶ ነው። ቀጣዩን የከፍተኛ ተቋም ትምህርቱን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመቀጠል ቢመዘገብም የሕይወት ዕጣ ፈንታው የመራው ወደ ቀድሞይቱ ሶቪየት ኅብረት ነው። በነፃ የትምህርት ዕድል።
ከሶቭየት ኅብረት ወደ ደቡብ ኢትዮጵያ

ጉዞ ወደ ሶቪየት ኅብረት Source: Supplied
አቶ አዳሙ በአገረ ሶቭየት ኅብረት የብሔራዊ ፕላን ምጣኔ ሃብት ትምህርታቸውን በሁለተኛ ዲግሪ ምረቃ እንዳጠናቀቁ ምልሰታቸው ያደረጉት ወደ አገር ቤት ነው።
አገር ቤት እንደተመለሱም በደቡብ ኢትዮጵያ የቀጣና ፕላን ጽሕፈት ቤት ረዳት የትራንስፖርትና መገናኛ ኤክስፐርት ሆነው ተመደቡ።

ሶቪየት ኅብረት Source: Supplied
እምብዛም ሳይቆዩ በዓመቱ የሲዳማ ክፍለ አገር የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ቁጥጥር ኮሚቴ ኮሚቴ ሶስተኛ የሥራ አስፈጻሚ አባል ሆኑ።
ስደትና ባሕር ማዶኛነት
እ.አ.አ በ1947 በምሥራቁ የሶሻሊስት ጎራና በምዕራቡ የካፒታሊስት ካምፕ የተጀመረው ቀዝቃዛው ጦርነት በካፒታሊስቱ ካምፕ በ1991 ድል ነሺነት ሲያከትም ለ17 ዓመታት ከሶሻሊስቱ ጎራ ወግኖ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) መንግሥት ዘመንም በኃይል ተገርስሶ አበቃ።
ኢሕዲሪ ሰልፉን ባስተካከለው የኢሕአዴግ ጊዜያዊ መንግሥት አገዛዝ ተተካ። እንደ አያሌ በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ አቶ አዳሙም ለስደት በቁ። የኬንያን ድንበር ተሻግረው ጥገኝነት ጠየቁ። ከጥቂት ወራት የኬንያ ስደት በኋላም በአውስትራሊያ ሰብዓዊ የስደተኞች ቅበላ ፕሮግራም ሳቢያ የአውስትራሊያ ነዋሪ ለመሆን ቻሉ።
የኑሮ ጅማሮ በአገረ አውስትራሊያ
የአገረ አውስትራሊያ ሥርዓተ መንግሥት አቶ አዳሙ ቀደም ሲል ከነበሩባቸው የሶቪየት ኅብረትም ሆነ የኢትዮጵያ ሶሻሊስታዊ ሥርዓታት የተለየ በመሆኑ ቅኝታቸውን ለማስተካከል ፊታቸውን ወደ ዩኒቨርሲቲ መለሱ። በቢዝነስ ምጣኔ ሃብት ትምህርት በሁለተኛ ዲግሪም ተመረቁ።
የኑሯቸውን የወደፊት አቅጣጫ በመልካም ጎኑ ቢቀይሱም የኬንያን ድንበር የተሻገሩትና አውስትራሊያንንም ሁለተኛ አገራቸው ያደረጉት ከባለቤታቸው ጋር አልነበረም። ያም በምናባዊ ምልሰት ወደ ቤተሰባቸው ካድማስ ባሻገር እንዲመላለሱ አድርጓቸዋል።

ምረቃ በአውስትራሊያ ዩኒቨርሲቲ Source: Supplied
የማኅበረሰብ አገልግሎት
አቶ አዳሙ ማለፊያ ከሚሏቸውና ከወላጆቻቸው ከወረሷቸው ዕሴቶች ውስጥ አንዱ ማኅበራዊና ሕዝባዊ ግልጋሎቶችን መስጠት በመሆኑ ለሶስት ጊዜያት በተደጋጋሚ የቪክቶሪያ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ ማኅበር ፕሬዚደንት ሆነው በመመረጥ ሁኔታዎች የፈቀዷቸውን ግልጋሎቶች አበርክተዋል።
ኢትዮጵያና አውስትራሊያ
አቶ አዳሙ “ኢትዮጵያና አውስትራሊያ ለእኔ አንድም የተለያዩም ናቸው” ቢሉም፤ ይላሉ። የአውስትራሊያ ኑሯቸውን የሚያዩት ከእሳቸው ዐልፎ ሁለት ልጆቻቸው ለባለ ሙያነት እንዲበቁ በረከቷን የቸረቻቸው መልካም አገር አድርገው ነው።
ኢትዮጵያና አውስትራሊያ ለእኔ አንድም የተለያዩም ናቸው
ለኢትዮጵያም በቀሪ ሕይወታቸው በተለያዩ ዘርፎች ግልጋሎታቸውን መለገስ ከወደፊት ውጥኖቻቸው ግንባር ቀደሙ ነው።