ወላጆች
የማርታ እናት ወይዘሮ አስረሱ በቀለ ይባላሉ። በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በሕክምና ሙያ የተሰማሩ ነበሩ። ዛሬም ድረስ በሕይወት አሉ። በጊዜያዊነት እየኖሩ ያሉትም እዚሁ አውስትራሊያ ከልጃቸውና የልጅ ልጆቻቸው ጋር ነው።

አባቷ ፀጋው ምንዳ - በውትድርናው ዘርፍ እስከ ሻምበል ማዕረግ ደርሰዋል። የውትድርና ተግባራቸውን ለመፈጸም ኤርትራ ዘምተው ሳለ መተኪያ የሌላት ውድ ሕይወታቸውን መተኪያ ለሌላት ውድ አገራቸው ኢትዮጵያ ለወቅቱ የአንድነት ትግል ያለ ስስት ሰውተዋል።

የትምህርት ዓለም
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተከታተለችው በኮልፌ የሰላም በር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ 12ኛ ደረጃ ያለውን ትምህርቷን ያጠናቀቀችው በኮልፌ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው።
በእናቷ የሕክምና መስክ መሰማራት ሳቢያ የልጅነት የቀለም ሕይወቷ ተጠቅሶ የነበረው ነርስ ወይም ሐኪም እንድትሆን ነበር። ያም ወደ ሳይንስ ትምህርት እንድታመዝን አድርጓታል። ይሁን’ጂ ወደ ዩኒቨርሲቲ ስትዘልቅ የገጠማት የጥናት መስክ የቋንቋና ሥነ ጽሑፍ ዘርፍ ነው።
ከትምህርት ቤት ወደ ጋዜጠኛነት
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማ ምሩቅነት በኋላ የሙያ ጅምሯ በኢትዮጵያ ራዲዮ ነበር። ሲልም፤ FM Addis 97.1 ሌላኛው የኢትዮጵያ ራዲዮ ልሳን ሆኖ ሲቋቋም ከመሥራቾቹ አንዷ ሆና ወደዚያ በመዞር ለሁለት ዓመታት አገልግላለች። በጥቅሉ ወደ አውስትራሊያ እስክታመራ ለአራት ዓመታት በራዲዮ ጋዜጠኛነት ሠርታለች።

ከኮልፌ ወደ አውስትራሊያ
የማርታ ወደ አገረ አውስትራሊያ አመጣጥ በጋብቻ ነው።

እንደማንኛውም አዲስ ሠፋሪ ከአዲሲቷ የመኖሪያ አገሯ አውስትራሊያ ጋር መላመድ፣ ራስን ከአገሬው የአኗኗር ዘይቤ ጋር ማዋደድ፣ የወጣትነት ሕልሞችን ዕውን ለማድረግ በእጅጉ ጉጉ የመሆን የሕይወት ጉዞ ውስጥ ከነተግዳሮቱና ስኬቱ አልፋለች።

የአገር ቤት የራዲዮ ጋዜጠኛነት መንፈሷ ሳይበርድ፤ የአውስትራሊያ የመጀመሪያ ሥራዋ የሆነው የልብስ ድርደራ - ፈታኝ የባሕር ማዶ ሕይወት ሽግግር ዕውነታ ሆኖ ውስጧን ፈትኖታል።
ከሁለት ዓመታት የባሕር ማዶ ሕይወት ወጀብ መዋለል በኋላም ቋሚ የመኖሪያ ፈቃዷን አገኘች። የመጀመሪያ ወንድ ልጇንም አቅፋ ሳመች። ገና ከአራስ ቤት ሳትወጣ ዳግም ራሷን በትምህርት የመለወጡ የተዳፈነ የጉጉት ፍም ነድዶ ወጣ። የመጀመሪያ ልጇን በወለደች ሶስተኛ ወሯ የዩኒቨርሲቲ በር አንኳኳች። ተቀባይነት አግኝታም ከRMIT በአስተርጓሚና ተርጓሚነት በዲፕሎማ ተመረቀች። እምባዛም ሳትቆይ በ Community Development ከቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን ተቀበለች።

በአውስትራሊያ ቆይታዋ ከትዳር ሕይወቷ የ14 - የ13 እና ስምንት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሶስት ወንዶች ልጆች እናት ሆናለች። የወደፊት ተስፋና ምኞቶቿ ከሚያርፉባቸው የሕይወት ንድፎቿ ቀዳሚዎቹ ልጆቿ መሆናቸውም እውነት ነው።

ተስፋና ምኞት
የማርታ ፀጋው - የወደፊት ተስፋና ምኞቶች የተቃኙት በቤተሰብና በአገር ሶስት ዋነኛ ትልሞቿ ዙሪያ ነው።
የመጀመሪያው - ልጆቿ በዕውቀት ጎልምሰው፣ ማለፊያ ሥራ ይዘው፣ ውጤታማ ዜጎች ሆነው ማየት፤
ሁለተኛው - በተሰማራችበት የሥራ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ሆና መዝለቅ ሲሆን፤
ሶስተኛው - ኢትዮጵያ ትልቅ የዕድገት ደረጃ ላይ ደርሳ ማየትና ለዕድገቷም በተቻለ መጠን በአንድ ዘርፍ አስተዋፅዖ ለማበርከት እችላለሁ የሚል ነው።
ማርታ ፀጋው - በአውስትራሊያ የ SBS አማርኛ ገዲብ ሪፖርተር ሆና እያገለገለች ትገኛለች። ለላቀው ሙያዊ አስተዋፅዖዎቿም አድናቆታችን ከፍ ያለ ነው።





